1K
ሐሰት፡ የኖርዌይ ትምህርት ተቋም (University of Oslo) ነጻ የትምህርት ዕድል አላቀረበም
የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ በሆነው ዋትስ አፕ በርካቶች የኖርዌይ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሆነው University of Oslo የነጻ ትምህርት ዕድል ስላቀረበ አመልክቱ የሚል መልዕክት እየደረሳቸው መሆኑን ተመልክተናል።
በምስሉ ላይ እንደሚታየው “የኦስሎ ዩኒቨርስቲ መሉ በሙሉ በነጻ ያቀረበውን የ 2021 የትምህርት ዕድል (Scholarship) ተጠቃሚ ለመሆን ያመልክቱ” የሚል መግቢያ ያለው መልዕክቱ የኦስሎ ዩኒቨርስቲ ባቀረበው በዚህ የነጻ ትምህርት ዕድል (Scholarship) ሙሉ በሙሉ የትምህርት ወጪ ፣ የመኖሪያ አበል ፣ ማረፊያ ክፍል ፣ የህክምና ወጪ ፣ የጉዞ አበል እና ያልተገደበ የስራ ፍቃድ ተጠቃሚ መሆን እንደሚያስችል ያትታል።
ከዚህ በታች በምስሉ ላይ እንደሚታየው የምዝገባ ሂደቱን ካጠናቀቁ በኋላ የቪዛ ፕሮሰስ ለመጀመር ስለ ትምህርት ዕድሉ “ለ15 ጓደኞችዎ ወይም 5 የዋትስ አፕ ግሩፕ” ላይ ማጋራት ግዴታ መሆኑን ይገልጻል።
ሆኖም አዲስ ሚዲያ በሀቅ ማንጠሪያ ክፍሉ በኩል ባደረገው ማጣራት ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኦስሎ (University of Oslo) ምንም አይነት የነጻ ትምህርት ዕድል (Scholarship) አለማቅረቡን አረጋግጧል።
ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኦስሎ (University of Oslo) በድረ-ገጹ ምንም አይነት የነጻ ትምህርት ዕድል (Scholarship) አለማቅረቡን ከላይ በምስሉ እንደሚታየው ገልጿል።
በሌላ በኩል በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በኖርዌይ “NLA” ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ቴርዬ ሼርዳል መረጃው ሃሰት መሆኑ የሚያረጋጡ ማሳያዎችን ገልጸውልናል።
-
የዋትስ አፕ ማስታወቂያው በግልጽ የቃላት ግድፈት አለው ለምሳሌ የተቋሙ ስያሜ “Oslo University” ሳይሆን “University of Oslo” ነው
-
የበጋ ትምህርት በኮሮና ወረርሺኝ ሳቢያ በኦንላይን እየተሰጠ መሆኑ
-
የበጋ ትምህርት የሚከታተሉ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን አለመቻላቸው ማስታወቂያው ሃሰት ለመሆኑ ማረጋገጫ እንደሆነ በኢሜል አሳውቀውናል።
This fact-check was produced by Addis Post in partnership with Code for Africa