698
ሐሰት ፡ ኢትዮ-ቴሌኮም 100GB ነጻ የኢንተርኔት ጥቅል እና የiPhone 13 pro ስልክ ሽልማት አላቀረበም
Eth tel co የሚል ስያሜ ያለው ፌስቡክ ገጽ የኢትዮ-ቴሌኮምን ስም እና አርማ በመጠቀም መስከረም 10 ፣ 2014 ዓ/ም (September 20, 2021) ኢትዮ ቴሌኮም 100 GB ነጻ የኢንተርኔት ጥቅል እንዲሁም iPhone 13 pro ስልክ ሽልማት ማቅረቡን የሚገልጽ ጽሁፍ አጋርቷል። ልጥፉ ብዙ ሰዎች ጋር ተደራሽ እንዲሆን ታቅዶ ለፌስቡክ በመክፈል ጭምር ማስታወቂያ አሰርቷል።
አዲስ ሚዲያ በሃቅ ማንጠሪያ ክፍሉ በኩል መረጃው ትክክል ነው? የሚለው ጉዳይ ላይ የማጣራት ስራ ያከናወነ ሲሆን ማስታወቂያው ሐሰት መሆኑን አረጋግጧል።
ከዚህ በታች በምስሉ ላይ እንደሚታየው የፌስቡክ ገጹ ጥቅምት 12 ፣ 2013 ዓ/ም (October 25, 2020) “Katawa” በሚል ስያሜ የተከፈተ ነው።
ገጹ በመስከረም 10 ፣ 2014 ዓ/ም ስያሜውን ወደ “Eth tel co” በመቀየር መለያ ምስሉን (Profile picture) ወደ ኢትዮ-ቴሌኮም አርማ ለውጧል። ስለ ገጹ በሚያትተው ክፍልም “mrcharmz1988@gmail.com” የሚል የኢሜል አድራሻ እና የፊሊፒንስ አገር መለያ ኮድ ያለው ስልክ ቁጥር ሰፍሮ ይገኛል።
“ታላላቅ ሽልማቶችን በማሸነፍ ደስ ይበላችሁ” ከሚል መግለጫ ጋር የ100GB ነጻ ኢንተርኔት ጥቅል እና iPhone 13 pro የማሸነፍ ዕድል ኢትዮ ቴሌኮም አቅርቧል በማለት በፌስቡክ ገጹ የሰፈረው የድረ-ገጽ ሊንክ ወደ ትክክለኛው የኢትዮ-ቴሌኮም ድረገጽ የሚወስድ አይደለም።
ትክክለኛው የኢትዮ ቴሌኮም የፌስቡክ ገጽም Ethio telecom የሚል ስያሜ ያለውና የፌስቡክ ማረጋገጫ ሰማያዊ ምልክት ያለው ሲሆን ከአንድ ሚሊየን በላይ ተከታዮች አሉት።
በዚህም Eth tel co በተባለ የፌስቡክ ገጽ ከኢትዮ ቴሌኮም እንደቀረበ ተደርጎ የተሰራጨው የሽልማት ማስታወቂያ ሐሰት ነው።