936
ሐሰት፡ ምስሉ በህወሓት ታጣቂዎች የተገደሉ እንስሳትን አያመለክትም
አርአያ ተስፋማርያም የሚል ስያሜ ያለው ከ 91ሺ በላይ ተከታዮች ያሉት የቲውተር አካውንት መስከረም 13 2014 አ/ም በህወሓት አማጺያን የተጨፈጨፉ እንስሳት ናቸው በሚል ከታች የተያያዘውን ምስል አጋርቷል።
ይሄ የትዊተር ጽሁፍ ከ 490 ጊዜ በላይ ሪቲዊት ተደርጓል።
አዲስ ሚዲያ ከኮድ ፎር አፍሪካ ጋር በመተባበር በሃቅ ማንጠሪያ ክፍሉ በኩል ባደረገው ማጣሪያ ምስሉ በህወሓት ኃይላት የተገደሉ እንስሳትን የሚያሳይ አለመሆኑን አረጋግጧል።
በግኝቱ መሰረት ምስሉ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት ተከትሎ “የህወሓት አማጺያን” እንስሳት ላይ ያደረሱት ጭፍጨፋ የሚያመላክት ሳይሆን እ.ኤ.አ በ 2017 “በኬኒያ ላኪፒያ አውራጃ በፖሊስ የተገደሉ እንስሳት” መሆናቸውንና ፖሊስ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ማለቱን በተመለከተ የተሰሩ ዘገባዎች አረጋግጠዋል።
ከላይ በምስሉ ላይ ከሚታየው ማረጋገጫ በተጨማሪ የጉግል ምስል ማሰሻ (Google reverse image search) ምስሉ ከአመታት በፊት ጥቅም ላይ መዋሉን ያሳያል።
በተጨማሪም በጥቅምት 23, 2010 በኬኒያው KTN የዜና አውታር የተሰራው የቪዲዮ ዘገባ እንስሳቱ በኢትዮጵያው ጦርነት የተገደሉ አለመሆናቸውን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።