978
ሐሰት፡ ፊልሰን አብዱላሂ ስልጣን ለመልቀቃቸው ዐብይ አህመድን በትዊተር ገጻቸው ተጠያቂ አላደረጉም
የሴቶች ፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ በ September 27, 2021 (መስከረም 17 ፣ 2014) ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ የደብዳቤውን ምስል በማያያዝ አስታውቀዋል።
ሚኒስትሯ የስራ መልቀቂያ ጥያቄ ማቅረባቸውን የሚገልጸውን የቲውተር መልዕክት ማጋራታቸውን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች የተሰጡበት ሲሆን በተባበሩት አረብ ኤምሬት የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ሱሌማን ደደፎ “ይሄ ውሳኔ ለምን በ 12 ኛው ሰዓት? አዲስ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ ለአንድ ሳምንት ለምን አልታገሱም?…“ በማለት ጥያቄ አዘል አስተያየት ሰጥተዋል።
“Cyberzena Citizen Journalists” የተባለ ከ 16ሺ500 በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጽ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ ለጻፉት አስተያየት ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ “አብይ በቀጣይ ሳምንት ከስልጣኔ የሚያነሳኝ ከሆነ ሳምንቱን ሙሉ በስራ መጠመድ አልፈልግም። ትንሽ ፈታ ማለት እፈልጋለሁ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል በማለት ከታች በምስሉ ላይ የሚታየውን መረጃ አጋርቷል።
አዲስ ሚዲያ ከኮድ ፎር አፍሪካ ጋር በመተባበር በመረጃው ዙሪያ የማጣራት ስራ አካሂዷል ፥ በዚህም አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ በሰጡት አስተያየት ላይ ሚኒስትር ፊልሰን ምንም አይነት ምላሽ አለመስጠታቸውን ተመልክተናል።
በተጨማሪም ከታች በምስሉ በግልጽ እንደሚታየው የሴቶች ፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ ትክክለኛ የቲውተር መለያ ስም (Username) እና አስተያየት እንደሰጡበት በማስመሰል የቀረበው የቲውተር አካውንት ስያሜ የተለያየ መሆኑን አረጋግጠናል።
በመሆኑም ከላይ የተገለጹትን ማስረጃዎች ዋቢ በማድረግ Addis Post Fact Check ፊልሰን አብዱላሂ ስልጣናቸውን ለመልቀቃቸው በምክንያትነት አቀረቡት የተባለውን አስተያየት አለመስጠታቸውን አረጋግጧል።
ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ በግል ጉዳያቸው ሳቢያ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን በደብዳቤው ከመግለጽ ውጪ ዝርዝር ምክንያት አላቀረቡም።